‎ራያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

‎ራያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያስተማራቸውን የቅድመ እና ድህረ ምረቃ ተማሪዎቹ የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ፣ የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ሃፍቱ ኪሮስን ጨምሮ የፌደራል እና ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ሰራተኞች፣ ተማሪዎች እንዲሁም የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ለ4ኛ ዙር በደማቅ ስነ-ስርዓት አስመርቋል።
‎ተመራቂዎቹ በኢንጅነሪንግ እና ቴክኖሎጂ፣ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ፣ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት፣ ተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ፣ ማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ ሰብ እንዲሁም በህግ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው።
‎በምረቃው ስነ ስርዓት የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ ለተመራቂ ተማሪዎችና ለተመራቂ ተማሪዎች ቤተሰብ በእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸው፤ ራያ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ፣ ለአከባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምር ስራዎች በማስፋፋት ውጤታማ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት እና ለዲጂታላይዜሽን የሚያግዙ ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ስራዎች ለመከወን ለሌሎች ተምሳሌት የሆኑ ስራዎች ለመስራት ትኩረት ሰጥተን እየሰራ ይገኛል በማለት በተለይ ዩኒቨርሲቲው በሃገራዊ የመውጫ ፈተናው እጅግ የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን፣ ዘርፈ ብዙ ግንባታዎች አከናውኖ ማስመረቅ መቻሉ፣ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ማስፋፋት፣ የግቢ ውበት ስራዎች፣ የቤተ ሙከራ እና ሰርቶ ማሳያ ፕሮጀክቶች ማደራጀት እንዲሁም በሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ከማስፋፋት አንፃር አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል በማለት ተናግረዋል።
‎ፕሮፌሰር ታደሰ አያይዘው ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልእክት፤ ተመራቂዎች ወደ ስራ ዓለም ስትሰማሩ ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ህዝባችሁን በቅንነት፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት እና ታማኝነት ማገልገል አለባችሁ ብለዋል።
‎በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር እና የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ በበይነ መረብ ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት፤ የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ፣ ከፍተኛ አመራሮች እና ማህበረሰብ ተቀናጅተን መንግስት በመደበልን በጀት በ2017 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው በ1.3 ቢልዮን ብር በጀት ስድስት የትላልቅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተሰርተው እንዲመረቁ፣ ዘመናዊ የመምህራን መኖሪያ ግንባታ እና የአስተዳደር ህንፃ ግንባታ እንዲፋጠን እና የዩኒቨርሲቲው ከፍታ ማስቀጠል ተችሏል ብለዋል፡፡
‎ዶ/ር ካሳሁን አክለውም፤ ተመራቂዎች በተማራችሁበት የትምህርት ዘርፍ በምትሰማሩበት የስራ ዘርፍ ጠንክራችሁ በመስራት ውጤታማ መሆን አለባችሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
‎የራያ ዩኒቨርሲቲ ዋና ሬጂስትራር ዳይሬክተር መምህር አብርሃ ተካ በምረቃው እንደገለጹት፤ በኢንጅነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ 59 ተማሪዎች፣ ህግ ትምህርት ቤት፣ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ 3 ተማሪዎች ፣ ተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ 7 ተማሪዎች፣ ማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ ሰብ ኮሌጅ 6 ተማሪዎች፣ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ 9 ተማሪዎች በድምሩ 90 ተማሪዎች በቅድመ ምረቃ ያስመረቁ ሲሆን 13 ተማሪዎ ደግሞ ከቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል ብለዋል።
‎በዩኒቨርሲቲው በፊዚክስ ትምህርት ክፍል የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ተማሪ ገብረመድህን ሓጎስ፤ ትምህርቴ ላይ ትኩረት በማድረጌ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኛለሁ በማለት በዩኒቨርሲቲው በቀሰምኩት ዕውቀት እና ክህሎት ሀገሬ እና ህዝቤን በቅንነት እና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።
‎በምረቃው ስነ ስርዓት በ2017 ዓ.ም ከመደበኛ ስራቸው በተጨማሪ ውጤታማ ስራ ያከናወኑ የህግ ትምህርት ቤት፣ የግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ እንዲሁም የጠቅላላ አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ የስራ ዘርፎች የዋንጫ ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡
‎ዩኒቨርሲቲው “ለተመራቂ ተማሪዎች እና የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች እንኳን ደስ አላችሁ!” ለማለት ይወዳል።