‎ራያ ዩኒቨርሲቲ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራቸው የነበሩ ስድስት ትላልቅ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በደማቅ ስነ ስርዓት አስመረቀ

‎በዩኒቨርሲቲው ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ግንባታቸውን ሲከናወኑ የቆዩት ስድስት ትላልቅ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዩ ዶ/ር አቡሌ ታከለ፣ የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ሃፍቱ ኪሮስ፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ሰራተኞች፣ ተማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በተገኙበት ዛሬ ሰኔ 13/2017 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት አስመርቋል።
‎በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ ስለ ፕሮጀክቶች ዝርዝር ማብራሪያ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በስድስት ወራት ውስጥ በ57 ሚልዮን ብር በጀት የተገነባው የውሃ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲትያችን ከነበረው አንድ የውሃ መስመር ዝርጋታ ከ 1.4 ኪ.ሜ በላይ በማስፋት አስተማማኝ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር ተደርጓል ብለዋል።
‎በተጨማሪ ከዋናው የከተማ አስፋልት መንገድ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚወስደውን አስቸጋሪ እና ለአደጋ የተጋለጠ የ700 ሜትር እርዝማኔ እና 21.5 ሜትር ስፋት ያለው መንገድ የአስፋልት እና ኮንክሪት ንጣፍ በማልበስ አጠቃላይ ወጪው ከ268 ሚልዮን ብር በላይ በጀት በማሰራት ለዩኒቨርሲቲው፣ አካባቢው ማህበረሰብ እና ለከተማው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው እንዲሆን አስችሏል ያሉት ፕሮፌሰር ታደሰ ከ315 ሚልዮን ብር በላይ በጀት ስድስት ኪሎሜትር የሚሸፍን አጥር እና 10.1 ሄክታር የሚሸፍን የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ ፕሮጀክት ከ14 ሚልዮን ብር በላይ በጀት ተሰርቶ በዛሬው እለት ለምረቃ በቅቷል ብለዋል።
‎ፕሮፌሰር ታደሰ አያይዘው እንደገለጹት 430 ሚልዮን ብር ለቤተሙከራ (Laboratory)፣ 167ሚልዮን ብር ደግሞ ለሰርቶ ማሳያ (Work Shop) ፕሮጀክቶች በመመደብ አስፈላጊ ግብኣቶች በማሟላት ለቤተሙከራ እና ለሰርቶ ማሳያ ህንጻዎቹ በ36 ሚልዮን ብር ጥገና እና እድሳት ተደርጓል ብለዋል።
‎ፕረዚደንቱ፤ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ስድስቱ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተጀምረው እስከሚጠናቀቁ ድጋፍና ክትትል ላደረጉ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ማኔጅመንት አባላት፣ ኮንትራክተሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች ድጋፍ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
‎በመርሀ ግብሩ የኢንጅነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ዲን መምህር ታደሰ ተክሌ እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ዓቅም የተደራጀው የሰርቶ ማሳያ (Work Shop) ማእከል የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እና በቴክኖሎጂው ዘርፍ የማህበረሰቡ ችግር የሚፈታ የሰው ሀይል ለማፍራት ትልቅ ዓቅም ይፈጥራል ብለዋል።
‎የጠብታ መስኖ (Drip Irrigation) ፕሮጀክት የተሻሻሉ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት፣ የግብርና ስራዎች ለማዘመን እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፋይዳው እጅግ የጎላ ነው ያሉት የግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲኑ መምህር ሞገስ አሰፋ ናቸው።
‎አቶ ሃፍቱ ኪሮስ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው በዛሬው ዕለት የተመረቁት ፕሮጀክቶች የዩኒቨርሲቲውን የትኩረት መስኮች ማለትም ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት፣ መረጃ ቴክኖሎጂ (IT) እና ህክምናና ጤና ሳይንስ ከግብ ለማድረስ እንዲሁም የመማር ማስተማር፣ የምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ዩኒቨርሲቲውን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ይረዳሉ ብለዋል።
‎የራያ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ፕሮጀክቶቹ ዩኒቨርሲቲው ራእዩን ለማሳካት፣ አገልግሎቱን ለማዘመንና የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ወደር-የለሽ እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና ስላላቸው በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሂደት ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት አመስግነዋል።
‎ፕሮጀክቶቹን መርቀው የከፈቱት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ፕሮጀክቶቹ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር፣ ማህበረሰብ አገልግሎት፣ አስተዳደር እና መሰረተ ልማት ዝርጋታ ዘርፍ የጀመረውን የለውጥ ጉዞ ወደ ፊት የሚያስቀጥሉ በመሆናቸው ይህን የተሳካ እንዲሆን ከላይ እስከ ታች ያለውን አመራር ተቀናጅቶ የሰራውን ውጤታማ ስራ ሊቀጥልበት ይገባል ብለዋል።
‎*****‎*****‎*****//*****‎*****‎*****
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ሰኔ 13/ 2017 ዓ.ም
‎ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
‎የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
‎*****‎*****‎*****‎*****//*****‎*****‎*****‎***