ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እና መካከኛ አመራሮች የኤሌክትሮኒክ የመንግስት ግዢ ስርዓት (E-GP) ስልጠና ተሰጠ።

ስልጠናው በማይጨው ከተማ ሸዊት ሆቴል ግንቦት 06/2016 ዓ/ም የተሰጠ ሲሆን በዩኒቨርሲቲያችን በ2017 ዓ/ም ዘመናዊ የሆነ የግዥ ፍላጎት፣ ዕቅድ እና መጠይቅ በመተግበር ውጤታማ የግዥ እና ፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ለማረጋገጥ ያለመ ነው፡፡
የራዩ ፕረዚደንት ተወካይ ነጋ ዓፈራ (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት በዩኒቨርሲቲያችን ግልፅ፣ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የመንግስት ግዥ አፈፃፀምና ንብረት አስተዳደር በማስፈን የመንግስትን ንብረት በጥንቃቄ የመያዝ፣ የመጠቀምና የመቆጣጠር እንዲሁም ንብረቱ አገልግሎቱ ሲያበቃ በወቅቱና በተገቢው መንገድ እንዲወገድ ለማስቻል ተግተን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ስልጠናው የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የግዥ ስራ አስፈፃሚ አቶ አብርሃ ካልኣዩ የግዥ ትርጓሜ፣ የግዥ ፈፃሚ አካላት ተግባርና ሀላፊነት፣ የግዥ ዘዴዎች እና ሂደት እንዲሁም በነባሩ የግዢ ስርዓት እያጋጠሙ የነበሩ ተግዳሮቶች ዙርያ ሰፊ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ መምህር የሆኑት መ/ር ብርሃነ ፀጋይ (ረ/ፕሮፌሰር) የኤሌክትሮኒክ የመንግስት ግዢ ስርዓት (E-GP) ምንነት፣ ታሪካዊ ዳራ፣ ዓላማ፣ ጠቀሜታ እና የግዥ ዘዴዎች ስልጠና የሰጡ ሲሆን በተለይ መ/ር ብርሃነ ፀጋይ አገላለፅ የዲጂታል የግዢ ስርዓቱ ትግበራ ወጪ እና ጊዜ የሚቀንስ፣ ጥራት የሚያረጋግጥ፣ ታማኝ፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነት የሚያሰፍን እንዲሁም ከወረቀት ነፃ የሆነ ስራ ለመስራት ያግዛል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እና ማብራርያ ተሰጥቷል፡፡