‎የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ለትውልድ ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ይበልጥ አጠናክረው ሊቀጥሉበት እንደሚገባ የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት ታደሰ ደጀኔ (ፕሮፈሰር) ገለጹ

“ትውልድ በመምህር ይቀረፃል ፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል!” በሚል መሪ ቃል የተካሄደውን የውይይት መድረክ በስኬት ተጠናቀቀ

‎ትምህርት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ልማትን ለማፋጠንና የአመለካከትና የአስተሳሰብ አድማስን ለማስፋት የምርምርና የፈጠራ ችሎታን ለማዳበር ለሀገር አንድነት እና ዕድገት ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን መሰረት በማድረግ ዩኒቨርሲቲው “ትውልድ በመምህር ይቀረፃል ፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል!” በሚል መሪ ቃል በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ጋር ግንቦት 15/ 2017 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ስማርት ክፍል ያካሄደውን የውይይት መድረክ በስኬት አጠናቀቀ።
‎የውይይት መድረኩ ቁልፍ ዓላማ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ቁርጠኛነት እና ርብርብ ለማቀናጀት እና ከምንም በላይ የማይተካ ሚና ያለውና በዘላቂነት የተሻለች ሃገርና ትውልድን የሚቀርፅ መምህርን ለማነቃቃት እንዲሁም በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ሀሳቦች ትኩረት አድርጎ ለመወያየት ነው፡፡
‎የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ የውይይት መድረኩ በይፋ የከፈቱት ሲሆን፤ የሀገር ዕድገት እና አንድነት የሚረጋገጥ በእውቀትና ክህሎት የታነጸ ትውልድ ማፍራት ሲቻል ነው በማለት ከትምህርት ማህበረሰብ ጋር መወያየት ስለ ሃገር እና ትውልድ መወያየት ስለሆነ ከውይይት መድረኩ ወሳኝ ትምህርት የምናገኝበት እና ሰፊ ውይይት የሚደረግበት ነው ብለዋል፡፡
‎የራያ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ልማት ምክትል ፕረዚደንት ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ የውይይቱ መነሻ ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት በትምህርት ሴክተሩ ሀገራዊ አንድነትንና ብዝሃነት የሚያከብሩ እና በመልካም ስነ-ምግባር የታነጹ ዜጎችን ለማፍራት፣ የትምህርት ተቋማትን ደረጃና ጥራት ለማሻሻል፣ የሥርዓተ-ትምህርት ተገቢነትና ጥራት ለማሻሻል፣ ፍትሃዊና አካታችና ተደራሽ የሆነ ትምህርትና ስልጠና ለማጐልበት፣ የከፍተኛ ትምህርት ኘሮግራሞችን ለማጠናከር፣ የራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎችን ለማጠናከር፣ የትምህርት ስርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እና ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲያበረክት የተሰሩ ስራዎች እንዲሁም በትምህርት ሴክተሩ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዝርዝር ገለፃ አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ክብሮም በገለፃቸው፤ መምህራን ጥልቅ ጥናት እና ምርምሮችን በማድረግ ለማህበረሰብ ለውጥ ማዋልና አወንታዊ ተጽዕኖ ማበርከት፣ መብትንና ግዴታን በሚገባ የሚረዳና በሚዛናዊነት የሚጠቀም ዜጋ መፍጠር እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለትምህርት ስራ ማዋል ይጠበቅባችኃል በማለት ተናግረዋል፡፡
‎በዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት እና ሁለቱም ምክትል ፕረዚደንቶች የተመራው ውይይት የተለያዩ ጥያቄ እና አስተያየቶች ተነስተው ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በመምህራን ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት፣ የደመወዝ ማነስ፣ የደረጃ እድገትና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች መብት አለመከበር፣ የመኖርያ ቤት እጥረት፣ የቤት አበል ማነስ፣ በተጨማሪ ስራዎች የሚገኝ ገቢ ላይ እና የስራ ግብር ክፍያ መብዛት፣ ለመምህራን እና ለቤተሰቦቻቸው የህይወት ኢንሹራንስ አለመኖር፣ የብድር አገልግሎት ችግር፣ የመምህራን ክብር ጥያቄ፣ የዝውውር መብት ጥያቄ፣ የሰላምና እና የፀጥታ ችግር በትምህርት ጥራት እያሳደረ ያለው ተጽእኖ እና ተያያዥ ጉዳዮች በውይይቱ ወቅት የተነሱ ሲሆኑ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረቶች እንደሚደረጉም የጋራ መግባባት ተፈጥሯል።
‎ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በመዝጊያ ንግግራቸው፤ መምህራን በውይይት መድረኩ ለነበራቸው ንቁ ተሳትፎ እና ትዕግስት ምስጋናቸውን በመግለፅ መምህራን ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት፣ መልካም ሥነ ምግባርን በማስተማር፣ ሃላፊነት የሚሰማቸውን ዜጎችን በማፍራትና ለሀገራዊ እድገት የሚተጉ ትውልድን በማነጽ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው እና የመምህርነት ሙያ የሙያዎች ሁሉ ቁንጮ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ አክለውም ይህን የተሳካ እንዲሆን ሁሉም መምህራን ለሙያቸው ክብር በመስጠትና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት የተቀናጀ መፍትሄ መሰጠት ያስፈልጋል በማለት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
‎ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከውይይቱ በኃላ እንደገለጹት የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ፣ ሁለንተናዊ ስብእና ያሟላ ትውልድ እንዲፈጠር እና የሀገር ዕድገት እንዲፋጠን የሚያስችል ውይይት መሆኑን አስተያየታቸውን በመስጠት በመምህራን በኩል የተነሱ ችግሮች በየደረጃዉ እንዲፈቱ የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማሳደግ እና ራስን በሙያ ብቁ እና ወቅቱ የሚፈልገውን ክህሎት መጨበጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
*****‎*****‎*****//‎*****‎*****‎**********
‎ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ግንቦት 15/ 2017 ዓ.ም
‎ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
‎የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት
‎*****‎*****‎*****‎*****//*****‎*****‎*****‎*****