የአመራር ብቃት እና ዓቅምን ለማሳደግ የአመራር ክህሎት ስልጠና ተሰጠ

‎የአመራር ብቃትና አቅምን ለማሳደግ ከደቡባዊ ትግራይ ዞን አስራ አራት ወረዳዎች ለተውጣጡ የወረዳ አመራሮች አካላት የአመራር ክህሎት ስልጠና በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህራን ከግንቦት 05 እስከ 06/ 2017 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት በዓዲ ሽሁ እና መኾኒ ከተሞች ተሰጥቷል።
‎ስልጠናው፤ ሳይንሳዊ የአመራር ክህሎት በመተግበር በዘርፉ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት እና የአመራር ብቃት እና ዓቅምን ለማሳደግ ያለመ ነው።
‎ስልጠናውን በይፋ ያስጀመሩት የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር መምህር ደባሲ ግደይ፤ የአመራር ክህሎት ብቃትና ዓቅምን ለማሳደግ በተዘጋጀው ስልጠና ላይ በንቃት በመሳተፍ የምንከተለውን የአመራር ሂደት የምናይበትና በቀጣይ የተሻለ እውቀትን እና ልምድ በመውሰድ ለውጥ የምናመጣበት የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
‎ስልጠናውን የሰጡት ዶ/ር መሐመድአወል የሱፍ በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶ/ር መሓሪ ሃይለ፣ ሳምሶን ተክለ (ረ/ፕሮፌሰር)፣ ቸኮለ ነጋሲ፣ ተክለሃይማኖት ገብረሃዋርያ እና ሰለሞን ለዩ ደግሞ የማኔጅመንት ትምህርት መምህራን ሲሆኑ ስልጠናው በዋናነት የአመራር ክህሎት ምንነት፣ ታሪካዊ ዳራ፣ ባህርያት፣ ዓይነት፣ እይታዎች፣ መርኆች፣ መሪነት እና ስራ አመራር፣ መሪ እና ሀላፊ፣ ዘመን ተሻጋሪ የመሪነት ክህሎት፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች እና ተግዳሮቶች፣ እንዲሁም በመሪነት ክህሎት የሚስተዋሉ ግጭቶች ምንነት፣ መንስኤዎች፣ የአፈታት ዘዴዎች እና የመፍትሔ ስትራቴጂዎች ሙያዊ ገለጻ የተደረገበት ነበር።
‎ስልጠናውን የሰጡት መምህራን፤ ስልጠናው ግልፅነት እና ተጠያቂነት ለማስፈን እና ህዝብ ለማገልገል በጠንካራ የቡድን መንፈስ ሁሉም ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችል እንደሆነና እንዲሁም ያገኙት ልምድና ክህሎት ልምዳቸውን ከትግበራ ጋር በማያያዝ እንዲያካፍሉ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
‎ከተሳታፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት በራያ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው የአመራር ክህሎት ስልጠና በዘርፉ የሚታየውን የአመለካከት ክፍተት ለመሙላት የተቀናጀ እና ተግባር ተኮር ስራ ለመስራት ግብዓት የተገኘበት መሆኑን የገለጹት የስልጠናው ተሳታፊዎች ለቀጣይም በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች ስልጠናው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
‎ስልጠናው ከዚህ በፊት አመራሩ በስራ ላይ የነበሩትን ጠንካራ ጎኖች የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና የነበረበትን ክፍተት ደግሞ ለይቶ በማውጣት ለቀጣይ የተቀናጀ የቡድን መንፈስ (Team Sprit) በማዳበር ውጤታማ ስራ ለመስራት የሚያነሳሳ እንደነበር ተሳታፊዎቹ ከስልጠናው በኃላ ተናግረዋል፡፡
‎*****‎*****‎*****‎*****//*****‎*****‎*****‎*****
‎ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ግንቦት 08 ቀን 2017 ዓ.ም
‎ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
‎የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት
‎*****‎*****‎*****‎*****//*****‎*****‎*****‎*****‎*****