‎‎የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የራያ ዩኒቨርሲቲ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የክረምት በጎ ፍቃድ የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ ይገኛሉ

‎የራያ ዩኒቨርሲቲ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በደቡባዊ ዞን ትግራይ በሚገኙ ዘጠኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የክረምት በጎ ፍቃድ የማጠናከሪያ ትምህርት ከሐምሌ 01 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች በአምስት የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች እየሰጡ ይገኛሉ።
‎ይህን በተመለከተ የራያ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የክረምት በጎ ፍቃድ የማጠናከሪያ ትምህርት በሚሰጥበት ትምህርት ቤቶች በመገኘት የሚመለከታቸው ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ ወላጆች እና ተማሪዎችን በማነጋገር የሚከተለው ዘገባ ሰርቷል።
‎የራያ ዩኒቨርሲቲ አዳሪ ትምህርት ቤት አስተባባሪ ዶ/ር ገብረመድህን ጎዲፍ እንደገለጹት የክረምት በጎ ፍቃድ የማጠናከሪያ ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ መሰጠት መጀመሩን ገልጸው የሁሉን ርብርብ የሚጠይቀውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን እና የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል ወሳኝ ነው ብለዋል።
‎በደቡባዊ ትግራይ ዞን ማሕበራዊ ጉዳይ የትምህርት ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት መምህር ሰማን ሞላ በበኩላቸው፤ በራያ ዩኒቨርሲቲ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እየተሰጠ ያለው የክረምት በጎ ፍቃድ የማጠናከሪያ ትምህርት ብቁ እና በስነ-ምግባር የታነጹ ዜጋን ለማፍራት በሚደረግ ሂደት የራሱ ሚና ያለው ሲሆን ሌሎች ተማሪዎችም የእረፍት ጊዜያቸውን እየተሰጠ ያለውን ትምህርት በመከታተል ለቀጣይ ትምህርታቸው እንዲዘጋጁ እና ወላጆች ልጆቻቸውን በየአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመላክ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
‎የክረምት በጎ ፍቃድ የማጠናከሪያ ትምህርት ከሚሰጥባቸው ትምህርትቤቶች መካከል በአላማጣ ከተማ የኮኸብ ፅባሕ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር የሆኑት መምህር ሕሉፍ አለማዮህ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
‎በማይጨው ከተማ ወፍሪ ሰላም ትምህርት ቤት እያስተማረች ያገኘናት ተማሪ ሰመር መሐመድ ፤ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ተማሪዎች እውቀታቸውን እና ክህሎታቸውን እንዲያጎለብቱ ጥሩ መሰረት ይጥላል ብላለች።
‎የክረምት ትምህርት መማራቸው የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያግዛቸው የገለጸው ደግሞ በማይጨው ከተማ ዘለአለም ደስታ ትምህርት ቤት በ7ኛ ክፍል የክረምት ትምህርቱን እየተከታተለ ያገኘነው ተማሪ ሃፍቱ ሓየሎም ነው።
‎በዓዲ ሽሆ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪዋ አርያም ካሕሳይ ደግሞ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት ለመጪው ዓመት የሚያግዘንን በቂ ዕውቀት እያገኘን ነው ብላለች።
‎በማይጨው ከተማ አለም ትምህሮት ቤት ልጁን እያስተማረ ያለው ወላጅ አቶ ግርማይ በርሀ፤ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን በመግለጽ መርሃግብሩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
‎*****//*****
‎ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ነሐሴ 10 ቀን 2017 ዓ.ም
‎ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
‎የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
‎*****//*****