ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ እና የትግራይ መምህራን ማህበር አመራሮች ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የትምህርት ክፍል የመምህራን ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት እና የራያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር አመራሮች ለመምረጥ በተካሄደ የምርጫ ሂደት ወቅት ነው።
በምርጫ ሂደቱ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው አካ/ምር/ቴክ/ሽግ/ማህ/ አገልግሎት ምክትል ፕረዚደንት ተወካይ ዶ/ር መሐመድአወል የሱፍ፤ የዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር ነጻ በሆነ መልኩ የመምህራንን ድምጽ የሚሰሙ፣ ሃሳብ በማቅረብና አቅጣጫዎች በመጠቆም የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እና የሃገርን እድገት ለመደገፍ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆን አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ዋና ፀሃፊ አቶ ጥላሁን ታረቀ በበኩላቸው፤ የማህበሩ ዓላማ ማብራሪያ ባቀረቡበት ወቅት የኢመማ ከተመሰረተበት 1940 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች እየተጋፈጠ የተለያዩ ስራዎች እየሰራ መጥቷል በማለት ማህበሩ የአባላቱ መብት ለማስከበር ብቻ ሳይሆን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ሙያዊ ግዴታን ለመወጣት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የትግራይ መምህራን ማህበር ፕረዚደንት ወ/ሮ ንግስቲ ጋረድ የመምህራን ማህበር ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ማህበር እና ሙሉ በሙሉ የመምህራን መብት ለማስከበር እየሰራ የሚገኝ መሆኑን ገልጸው ይህን እንዲሳካ መምህራን በተደራጀ መልኩ ማህበራቸው እንዲያጠናክሩ የክልሉ መምህራን ማህበር በበኩሉ የመምህራን ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚችለውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚጥርም አረጋግጠዋል፡፡
ይህን መሰረት በማድረግ ከተወካይ መምህራን ጋር በተካሄደው ውይይት የመብት እና አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ተነስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን የማህበሩ መጠናከር የመምህራንን ጥያቄ በተደራጀ መልኩ ለመመለስ፣ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እና የሃገሪቱን እድገት ለማቀላጠፍ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተመላክቷል።
በመጨረሻም በተካሄደው ሰባት አባላት ያካተተ የራያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር አመራር ምርጫ፤ ፕረዚደንት መምህር አብርሃ ሕሉፍ ከኢንጅነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ፣ ምክትል ፕረዚደንት መምህር ግርማይ ሃይለኪሮስ ከማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ ሰብዕ ኮሌጅ፣ ፀሃፊ ደግሞ መምህርት ለተብርሃን ገብረሂወት ከኢንጅነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የተመረጡ ሲሆን የተመረጡ አመራሮች ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ በሆነ መልኩ የተጣለባቸውን ሙያዊ ሃላፊነታቸው እንዲወጡ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ተገልጿል።









*****//*****
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ መጋቢት 30/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
*****//*****