ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ህዳር 19/ 2018 ዓ/ም
በየአመቱ ህዳር 22 የሚከበረው ዓለም አቀፍ የኤች አይ ቪ ኤድስ (HIV/AIDS) ቀንን ምክንያት በማድረግ የራያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዛሬ ህዳር 19/ 2018 ዓ/ም በራያ ዩኒቨርሲቲ የውውይት መድረክ አካሂዷል።
የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በደቡባዊ ትግራይ ዞን ብሎም በትግራይ ክልል የኤች አይ ቪ ኤድስ (HIV/AIDS) ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አብራርተው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከተለመደው አካሄድ በተሻለ የመፍትሔ መንገድ ካልተከተሉ አደጋው አሁንም የባሰ እንደሚሆን አሳስበዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም በሽታው በትግራይ ቀድሞም ቢሆን አስከፊ ጉዳት እያደረሰ እንደነበረ አውስተው ከጦርነቱ ብኃላ ደግሞ የበሽታው ስርጭት ሲባባስ በአንፃሩ ማሕበረሰቡ ስለ በሽታው የነበረው ግንዛቤና የሚያሳየው ጥንቃቄ ግን በጣም እንደቀነሰ ገልፀዋል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ ማሕበረሰብ ጉድኝንት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተ/ሳይንትፊክ ዳይሬክተር መሓሪ ሃይለ (ዶ/ር) በበኩላቸው የበሽታው እንደ አዲስ ማገርሸት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ እና ያንን ለመግታት ደግሞ ዩኒቨርሲቲው ከማሕበረሰቡና ሌሎች ባለድርሻ ኣካላት ጋር አብሮ ለመስራት እንዲረዳ ዘንድ መድረኩን እንደተዘጋጀ ገልፀዋል።
የበሽታው ምንነት፣ ዳግም የማገርሸቱ ምክንያቶች፣ በማሕበረሰቡ እያደረሰው ያለ ጉዳት ኣሳሳቢነትና የበሽታው ስርጭት ለመግታት ባለ ድርሻ አካላት ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ተግባራትን የሚመለከቱ ሁለት ጥናታዊ ፅሁፎች በራያ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን እና ከትግራይ ጤና ቢሮ በመጡ ባለሙያዎች ተዘጋጅተው ጥልቅ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በሽታው በደቡባዊ ትግራይ ወረዳዎች፣ በተለይ ደግሞ ታዳጊ ከተሞች እና የገጠር ወረዳዎች ላይ በተካሄዱ ዳሰሳዎች መሰረት በሽታው እስከ 12% መድረሱን ተመላክተዋል።
በውይይት መድረኩ የዩኒቨርሲቲያችን ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የትግራይ ጤና ቢሮ ተወካዮች፣ የዞኑ እና የዞኑ ወረደዎች የጤና ቢሮ ኃላፊዎችና መኮንኖች፣ የተለያዩ የኤች አይ ቪ ኤድስ (HIV/AIDS) መከላከል አደረጃጀቶች፣ የዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።
በመድረኩ የበሽታው ስርጭት ለመግታት በዞኑ በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገቡ ዝርዝር እርምጃዎች ዙርያ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን እርምጃዎቹን ለማስተባበር ደግሞ የራያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሚመሩት ግብረ-ኃይል በማቋቋም መድረኩ ተጠናቋል።
*****//*****
ዕውቀት ለማህበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
*****//*****
የዩኒቨርሲቲያችን መረጃዎች ለማግኘት እነዚህን አማራጮች መጠቀም ይችላሉ:-
YouTube: https://www.youtube.com/@RAYAUNIVERSITY
Twitter: https://x.com/RayaUn2008
Website: https://www.rayu.edu.et/
P.O. Box: 92, Maichew

Users Last 7 days : 816
Users Last 30 days : 2619
Total Users : 27005