ዓለም አቀፉ የጸረ-ሙስና ቀን “ትውልድን በሥነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ቃል በራያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል

(ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ሕዳር 22 /2018 ዓ.ም)
በራያ ዩኒቨርሲቲ የስነ ምግባር መከታተያ ስራ አስፈፃሚ አዘጋጅነት 22ኛው የዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን “ትውልድን በሥነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ቃል ዛሬ ህዳር 22 /2018 ዓ/ም በተለያዩ መርሐግብሮች በራያ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በበዓሉ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት፤ ሙስና እንደ ሀገር ውድቀት የሚያስከትል የልማት እንቅፋት በመሆኑ ይህን ብልሹ አሰራር በቁርጠኝነት ለመከላከል ትውልዱን በሥነ-ምግባር በማነጽ እና ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግ ከሙስና የጸዳ ተቋማዊ አደረጃጀት በማቋቋም እንዲሁም ልዩ ልዩ አሰራሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የጸረ-ሙስና ቀን ዓላማውን እና የበዓሉን አከባበር አስመልክተው ሀሳብ የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ካሕሱ ቦለድ በበኩላቸው፤ ሙስናን መከላከል ካልተቻለ የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ማስቀጠል ስለማይቻል ሙስናን የሚፀየፍ ጤናማ ማህበረሰብና ትውልድን በመፍጠርና ጠንካራ ተቋም በመገንባት እንዲሁም ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ኃላፊነታቸው ሊወጡ እንደሚገቡ አስገንዝበዋል።
ሙስናና ብልሹ አሰራሮች በሀገራችን እና በህዝባችን ላይ የሚያደርሰውን ኢኮኖሚዊ፣ ማህበራዊና ፓለቲካዊ ቀውስ ለመከላከል ከህብረተሰቡ ጋር በአንድነት ለመታገል በማሰብ ቃላችንን የምናድስበት እና የፀረ ሙስና ትግሉ ለማጠናከር ተቋማትን በዲጅታል አሰራር ለማዘመን በትኩረት መስራት ይገባል ያሉት ደግሞ የራያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ነጋ ዓፈራ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ሙስና ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ውድቀት የሚያስከትል ልዩ ትኩረት የሚጠይቅ አንገብጋቢ አጀንዳ መሆኑን ለማንፀባረቅ እና የጸረ ሙስና ትግሉ ህዝባዊ ለማድረግ ከፌደራል የተላከ ፅሁፍ በተለይ በፋይናንስ አስተዳደር፣ በግዥ ሂደት፣ ንብረት አያያዥ፣ ግብር አሰባሰብ፣ ተቋሟዊ አሰራር እና በሌሎች አስተዳደራዊ ዘርፍ የሚስተዋሉ አስተዳዳራዊ ክፍተቶች እና የሙስና ተግባራት ቀርበው ውይይት ተደርጎበታል።
የደቡባዊ ትግራይ ዞን የጸረ ሙስና ኃላፊ አቶ ኪሮስ አብርሃ የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ በማጠናከር፣ የተቋማትን አሰራር በማዘመን፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እና በቅንጅት በመሥራት እንዲሁም በዓሉን ስናከብር የሙስናን አስከፊነት በመረዳት ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ሁሉም አጋዥ እንዲሆን አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም የራያ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ማለትም ፕሬዚደንት እና ሁለቱም ምክትል ፕሬዚደንቶች የሃብት ማስመዝገብያና ማሳወቅያ ሰነድ ከፈረሙ ብኃላ የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሃይለኪሮስ ከበደ ዓለም አቀፉ የጸረ-ሙስና ቀንን ምክንያት በማድረግ ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ ቀርቧል።
የዘንድሮ የጸረ-ሙስና ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ22ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ “ትውልድን በሥነ ምግባር ፤ ተቋምን በአሰራር!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል።
“ትውልድን በሥነ ምግባር፤ ተቋምን በአሰራር!”
==============================
እውቀት ለማህበረሰባዊ ለውጥ!
ራያ ዩኒቨርሲቲ
የህዝብና አለምቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
*************************