በራያ ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትሥሥር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ሥር የሚገኝ የሥራ ፈጠራ ልማት (Entrepreneurship Development) ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አዘጋጅነት ለ2017 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች እና ሳይንስ ሼርድ ተማሪዎች ለማስረፅ የስራ እድል ፈጠራ እውቀትና ክህሎት ለማሳደግ ያለመ የኢንተርፕሪነርሽፕ የማነቃቅያ ስልጠና (Entrepreneurship Motivational Training)፤ ዓለም አቀፍ የስኬታማ ሥራ-ፈጣሪዎች ብቃቶችና ባህርያት፣ የቢዝነስ ዕቅድ አዘገጃጀት፣ የህይወት ክህሎት እንዲሁም በሀገራችን ያሉ የቢዝነስ አማራጮችና የመንግስት ድጋፍና የአሰራር ስርዓት በሚሉ ርዕሶች ለሁለት ተከታታይ ቀናት ከግንቦት 16-17 /2017 ዓ.ም በራያ ዩኒቨርሲቲ ተሰጥቷል፡፡
ስልጠናው በዋናነት ተመራቂ ተማሪዎች የስራ ፈጠራ ባህላቸው በማዳበር ራሳቸው እና ማህበረሰባቸው ለመጥቀም እና ሥራ ፈጣሪዎች ለመሆን ያላቸውን ዕቅድ፣ ዕውቀት እና ክህሎት በማቀናጀት ከተቀጣሪነት ወደ ስራ ፈጣሪነት ለማሸጋገር ያለመ ነው፡፡
መምህርት አስመረት ኪዳነ፣ ዶ/ር ሃፍቱ አረፈ፣ ዶ/ር መሐሪ ሃይለ፣ ዶ/ር አለም ገ/መድህን፣ ዶ/ር ረዳኢ ካሕሳይ እና ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃነ ፀጋይ ለተመራቂ ተማሪዎች እና ሳይንስ ሼርድ ተማሪዎች ስልጠና የሰጡ ሲሆን ስልጠናው በርካታ ወጣቶች ላሏት ሃገራችን እና እየጨመረ ለመጣው የሥራ ፈጠራ ለውጥ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው በመግለፅ ተማሪዎች አከባቢን በአግባቡ በመቃኘት፣ ምቹ የስራ እድሎችን እና አጋጣሚዎችን በመለየትና አስፈላጊ ግብአቶችን በመጠቀም ወደ ትግበራ በመግባት የማህበረሰቡን ችግር ፈቺ በመፍጠር አርአያ መሆን ይገባችኃል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ተማሪዎቹ በራሳችው ተነሳሽነት ያሉትን መልካም አጋጣሚዎችን በመለየት ያገኙትን ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም ውጤታማ ስራ በመስራት፣ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት አስፈላጊውን መፍትሔ በማሰቀመጥ ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅና ማላመድ፣ ሀብት ማፍራት እና ማስፋፋት እንዲሁም የስራ ፈጠራ ባህል ማዳበር ያለባቸው መሆኑን አስገንዝቧል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ማዕከሉ ዩኒቨርሲቲው በስራ ፈጠራ ክህሎት አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲራመድ ለማድረግ፣ ሰዎች ያላቸው እምቅ የፈጠራ ክህሎት ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲቀይሩ ለማስቻል፣ የአከባቢያችን ብሎም የሀገራችን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ፣ በመማር ማስተማሩ ሂደት እሴት ሊጨምሩ የሚችሉ እንዲሁም ወደ ህብረተሰቡ ሊሸጋገሩ የሚችሉ የተለያዩ የፈጠራ ክህሎት ያላቸው ሰዎች በመለየት የፈጠራ ችሎታ ወይም የንግድ ሥራ ተሰጥኦ ውድድር ለማቅረብ የሚያስችላቸው የቢዝነስ ዕቅድ አዘገጃጀት ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ሰልጣኞቹ የሚከተለዉን አስተያየት ሰጥተዋል።
ተማሪ ቅሳነት ሃይላይ ከሳይንስ ሼርድ እንደተናገረችው በዓላማችን ፀንተን ስራ እንዴት መፍጠር እንዳለብን እና የስራ ፈጠራ ባህል እንዴት ማዳበር እንደምንችል በጥሩ የስልጠና አቀራረብ ተሰጥተናል ብላለች።
የማኔጅመንት ትምህርት ክፍሉ ተመራቂ ተማሪ ናሆም ሓለፎም ተመራቂ ተማሪዎች ከመንግስት ስራ ይልቅ በዙሪያችን ያለውን ዕድል ተጠቅመን የራሳችን ስራ በመፍጠርና ስራ አጥነትና ህገ ወጥ ስደትን በማስወገድ እንዲሁም ከአደንዛዥ ዕፆች ራሳችን በመጠበቅ ማህበረሰብን ለማገልገል ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የስራ ፈጠራ እና የህይወት ክህሎት ስልጠናው ተመራቂዎች ከትምህርት ወደ ሥራ እንዲሸጋገሩ በማድረግ በኩል ትልቅ ጥቅም እንዳለው በመግለፅ የሚሰጡ ስልጠናዎችም ተግባር ተኮር እና ተከታታይነት ባለው መልኩ መሰጠት እንዳለባቸው የገለፀው ደግሞ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ተመራቂ ተማሪ ሃ/ማርያም ተ/ማርያም ነው፡፡
ተማሪ ናትናኤል ሰለሞን ከሳይንስ ሼርድ፤ በህይወታችን የተለያዩ አጋጣሚዎችን ተጠቅመን የሚያጋጥሙን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በማለፍ የራሳችንን የስራ ፈጠራ ሀሳብ በማመንጨት አዲስ ነገር ፈጥረን በመስራት የራሳችንና የማህበረሰቡን ህይወት በማሻሻል ረገድ ስልጠናው መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ሀሳቡን ገልጿል፡፡
ተማሪ አሸናፊ አባዲ ከሳይንስ ሼርድ በበኩሉ ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀላቸው የስራ ፈጠራ እና የህይወት ክህሎት ስልጠና ጠቃሚ ግንዛቤ ያገኙበት በመሆኑ ስልጠናው ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብሏል፡፡
በመጨረሻም ተመራቂች ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ ተመርቀው ሲወጡ ወደ ስራው ዓለም ለመቀላቀል እና የራሳቸውን ስራ ፈጥረው እንዲሰሩ በማሰብ የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን የገለፁት የጽ/ቤቱ አስተባባሪ መምህር ተክለሃይማኖት ገብረሃዋርያ፤ ተመራቂዎች በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም ስነ-ምግባር ብቁ በመሆን ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ፣ በዙሪያቸው ያሉትን አማራጮች እንዲጠቀሙና ማህበረሰባቸው እንዲያገለግሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡









