በዩኒቨርሲቲው ዘርፈ ብዙ የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂ (ICT) መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እየተከናወኑ ነው

ራያ ዩኒቨርሲቲ የዘመናዊነት (Digitalization) ጉዞውን ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂ (ICT) መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እያከናወኑ የሚገኙ ሲሆን በተለይ የመስመር እና በይነ መረብ የፌደራል እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ማለትም የመውጫ ፈተና (Exit Exam) ፣ የ12 ኛ ክፍል፣ E-SHE፣ E-LEARNING፣ ብሄራዊ የድህረ ምረቃ መግቢያ ፈተና (NGAT) ፈተናዎች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ለሚሰጡ ፈተናዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ መፈተን የሚያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ትኩረት ያደረገ ነው።
የዩኒቨርሲቲው የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂ ሥራ አስፈፃሚ መምህር ቢንያም ወልደገብርኤል እንደተናገሩት፤ የመሰረተ ልማት ዝርጋታው በበይነመረብ ከማስተማር እና ከመፈተን ባሻገር ተማሪዎች በሚማሩትን ትምህርት ለመብቃት የፈለጉትን የትምህርት መረጃ እና መርጃ መፃህፍት መርጠው እንዲከታተሉ እና ለተለያዩ የምርምር ስራዎች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።
መምህር ቢንያም አክለው እንደገለፁት፤ በአሁኑ ሰዓት በ26 የኮምፒተር ላብ ማእከላት በአንድ ጊዜ 910 ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች ማስተናገድ የሚችል የኔትወርክ ዝርጋታ፣ አስፈላጊውን የቁሳቁስ የማሟላት ሥራ፣ የግዢ ስራ እንዲሁም የዓቅም ግንባታ ስራዎች ተሰርቷል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በበኩላቸው፤ የመሰረተ ልማቱ ዝርጋታ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በምናደርገው መሰረታዊ ለውጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በመግለፅ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር በበይነ መረብ የሚፈተኑ 668 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲያችን እንዲፈተኑ የመደበ ሲሆን ዩኒቨርሲቲውም አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ እየተጠባበቀ ይገኛል ብለዋል።
****************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ሚያዝያ 09/ 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ
****************************************