ትምህርት ሚኒስቴር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ እንደ ሀገር ተፈጻሚ እንዲሆኑ ለታቀዱና ተፈጻሚ እየሆኑ ለሚገኙ የሪፎርም አጀንዳዎች ስኬት እውን ለማድረግ የሕዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ሥራዎች ሚና ለማጉላት መጋቢት 27-28/ 2017 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደውን የመንግሥት ዩኒቨሲቲዎች የሕዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚዎች ፎረም በስኬት ተጠናቀቀ፡፡
በፎረሙ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም እንደገለጹት፤ ያለንበት ጊዜ የመረጃ ፍሰት ፈጣን የሆነበትና ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት በመሆኑ በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የኮሚዩኒኔሽን ለማጠናከር ፎረሙ በዘርፉ ያለውን መልካም ተሞክሮ እንዲያጋራ፣ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጠንካራ ሥራዎችን ልምድ እንዲቀስም ብሎም ቀጣይ ዘላቂ ግንኙነቶችን እንዲያጠናክር ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሀገራችን የትምህርት ዘርፍ ከገጠመው ስብራት እንዲወጣ ለማስቻል በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል በርካታ የሪፎርም አጀንዳዎች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን የተናገሩተ በትምህርት ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ተፈራ፤ የሪፎርም አጀንዳዎቹ ስኬታማና ውጤታማ ለማድረግ ጠንካራ የሕዝብ ግንኑነትና ኮሚዩኒኬሽን ሥራ የሪፎርም አጀንዳዎች ተክትለው መከናወን አለባቸው ብለዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ቦጋለ፤ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ ተቋም ራዕይ፣ ዓላማ እና የሚያከናውናቸውን ተግባራት መሠረት በማድረግ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለአንድ ተቋም ስኬት ወሳኝ ሚና ያለው ዘርፍ መሆኑን ያስረዱት የዘርፉ ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲያበረከቱ አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለ ስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳምሶን መኮንን በበኩላቸው፤ “Contemporary PRs Communication Strategy” በሚል ርዕስ ባቀረቡት፤ ገለጻ ዘመኑ የቴክኖሎጂና የኮሚዩኒኬሽን እንደ መሆኑ ሚዲያ ላይ ራሱን ያልሸጠና በሚዲያ የተሸነፈ ሀገርም ሆነ ተቋም የትም መድረስ አይችልም በማለት በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ኃላፊዎች ከሚዲያዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር፣ የገጽታ ግንባታ ስትራቴጂ ማዘጋጀት፣ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞችን መጠቀምና በየጊዜው ወቅታዊ ማድረግ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞችን ቬሪፋይ ማስደረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የፎረሙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በመድረኩ የሁለት ቀናት ቆይታ በርከት ያሉ አዳዲስ ተሞክሮዎች የቀሰሙበት፣ እርስ በእርስ ልምድ የተለዋወጡበት፣ ከቀረቡ ገለጻዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሕዝብ ግንኙነት ሥራን ለማጠናከርና የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚያስችሉ አዳዲስ ዕውቀቶችን ያገኙበት መሆኑን ተናግረው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ፎረሙ በተሳካ ሆኔታ እንዲካሄድ ላደረገው የላቀ ሚና ምስጋናቸውን ችረዋል፡፡
በፎረሙ የተለያዩ አጀነዳዎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን በመድረኩ ማጠቃላያ የፎረሙ ተሳታፊዎች የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን እና የአርባ ምንጭ አዞ እርባታ ጣቢያን ጎብኝተዋል፡፡









*****//*****
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ መጋቢት 29/ 2017 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት
*****//*****