ለዩኒቨርሲቲው የዓቅም ማሻሻያ ትምህርት መርሀ ግብር (Remedial Program) ፈታኝ መምህራን እና ተፈታኝ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ሀላፊዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ ሥራ አስፈፃሚዎች እና አስተባባሪዎች በተገኙበት በዩኒቨርሲቲው መሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም የሚመለከታቸው አካላት የፈተና አሰጣጥ ሂደት ገለጻ (Orientation) ተደርጓል።
የገለጻው ቁልፍ ዓላማ ተማሪዎች እና መምህራን በፈተና ሂደቱ ሊተገብሯቸው የሚገቡ ቁልፍ ተግባራት ግንዛቤ በማስጨበጥ የተሳካ የፈተና ሂደት ለመተግበር እና የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ነው።
ራያ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር ዘርፍ ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑን ያወሱት የዩኒቨርሲቲው ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ፤ የተቀናጀ የፈተና ሂደት ተከትለን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለን የተቀበልናችሁ ተማሪዎቻችን በጥሩ ስነ ምግባር ተፈትናችሁ ጥሩ ውጤት አምጥታችሁ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንድትገቡ ለማስቻል በመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፈተናዎች ማእከል አስተባባሪ መምህር ተስፋይ ሀረገ-ወይን፤ የዓቅም ማሻሻያ ትምህርት ሲወስዱ ቆይተው ለሚፈተኑ ተፈታኞች ስለፈተናው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ተፈታኞች በፈተና ሂደቱ ማድረግ ያለባቸውን ዝርዝር ተግባራት ገለጻ አድርገዋል።
አጠቃላይ የፈተናው ማብራሪያ የሰጡት የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዩ ዶ/ር አቡሌ ታከለ ሲሆኑ ተፈታኞች የዩኒቨርሲቲውን መልካም ገፅታ ለማስቀጠል የፈተና ህጎችን ተከትላችሁ መፈተን አለባችሁ ብለዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎቹ በራስ መተማመንን አዳብረን ለውጤት እንድንበቃ በዩኒቨርሲቲው የተከወኑ የተለያዩ ክንውኖች መሰረት አድርገን ዘንድሮ በሚሰጠው ሀገር አቀፍ የዓቅም ማሻሻያ ትምህርት መርሀ ግብር (Remedial Program) ፈተና ጥሩ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል ያሉት ደግሞ ተፈታኞች ናቸው።
በመጨረሻም እንደ ዩኒቨርሲቲው የፈተናዎች ማስተባበሪያ ማእከል መረጃ መሰረት በዩኒቨርሲቲው በ2017 የትምህርት ዘመን ከ አንድ ሺ ሁለት መቶ ተማሪዎች የዓቅም ማሻሻያ ትምህርት መርሀ ግብር (Remedial Program) ፈተናን እንደሚወስዱ ለማወቅ ተችሏል።






***************//***************
ራያ ዩኒቨርሲቲ ፤ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት
***************//******************************