በዩኒቨርሲቲው የራያ ባህል እና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ጥናት ማዕከል ለመመስረት የምክክር መድረክ ተካሄደ።

በዩኒቨርሲቲው የራያ ባህል እና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ጥናት ማዕከል ለመመስረት የትግራይ ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም፣ የትግራይ ደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ሃፍቱ ኪሮስ፣ የትግራይ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ፅ/ቤት ሃላፊ ዶ/ር ከላሊ አድሀና፣ የራዩ ፕረዚደንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ፣ የራዩ አስተዳደርና ልማት ም/ል ፕ/ት ዶ/ር ክብሮም ካሕሱ፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ል ፕ/ት ዶ/ር እያሱ ያዘው፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ልማት ም/ል ፕ/ት ዶ/ር ተከስተ ብርሃኑ፣ የዘርፉ ሙሁራን እና ባለሙያዎች፣ የትግራይ ደቡባዊ ዞን ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ሀገር ሽማግሌዎች፣ ሀይማኖት መሪዎች፣ እና ሚድያ አካላት በተገኙበት ሚያዝያ 19/2016 ዓ/ም የምክክር መድረክ ተካሄዷል።
የውይይት መድረኩን ያስጀመሩት ፕ/ር ታደሰ ደጀኔ ለተሳታፊዎች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ራዩ የሰራቸው አንኳር ስራዎች አብራርተዋል።
አቶ ረዳኢ ሓለፎም “የራያ ባህልና አብሮነት እሴት” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ሀሳብ ራያ እና የራያ ማህበረሰብ ድንቅ ባህል፣ የቱሪዝም መስህቦች፣ ጥበብ፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ታሪክ እና እሴት ያለው በመሆኑ ይህ በራዩ የተቋቋመ ማእከል ጥናት እና ምርምሮች በማካሄድ ውጤታማ ስራ መሰራት አለበት ብለዋል።
የማእከሉ ዓላማ የራያ ማህበረሰብ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ፣ ኪነ-ጥበብ፣ ታሪክ፥ ቅርስ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ባህል፣ ሀገር በቀል ዕውቀት፣ የአኗኗር ዘይቤና እሴቶችን ትኩረት አድርጎ የሚሰራና የሚያስተዋውቅ እንዲሁም ከሳይንሳዊ ዘዴዎች ጋር በማቀናጀትና በማዘመን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ነው።
በራዩ የማህ/ዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ ፅሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ካሕሳይ ቸኮለ (ረዳት ፕሮፌሰር) አምስት ክፍሎች የያዘ የማእከሉ የውስጥ አሰራር መመሪያ በዋናነት የማዕከሉ ተልዕኮ፣ አደረጃጀት፣ ተግባርና ኃላፊነት፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የአሰራር ማዕቀፍ፣ የዩኒቨርሲቲው የተለያዩ አካላት ተግባር እና ኃላፊነት፣ የክትትል እና ግምገማ ስርዓት ዝርጋታ፣ በትብብር የሚሰሩ ስራዎች፣ የገቢ አሰባሰብ እና አጠቃቀም፣ መመሪያውን ስለማሻሻል እና የሚፀናበት ሁኔታ ማብራርያ ሰጥተዋል።
መ/ር ካሕሳይ ቸኮለ ባደረጉት ገለፃ ዩኒቨርሲቲው የራያ ማህበረሰብ ባህላዊ አለባበስ፣ ጭፈራዎች እና እስክስታዎች፣ ጨዋታዎች፣ የጸጉር አሰራር፣ የምግብ እና የመጠጥ አዘገጃጀት፣ መዋብያዎች፣ ሥነ-ቃል፣ ሥነ-ፅሁፍ፣ የግጭት አፈታት ዘዴዎች፣ የዕርቅ ሥነ-ስርዓት፣ መድሃኒቶች፣ የእጅ ጥበብ፣ ቅርስ፣ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መስህቦች፣ ሃይማኖታዊ ቦታዎች ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በባህል ማእከሉ ምስረታ ዙርያ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በአቶ ረዳኢ ሓለፎም፣ ዶ/ር እያሱ ያዘው እና መ/ር ካሕሳይ ቸኮለ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
************************************************
ራያ ዩኒቨርሲቲ
ሚያዝያ 19/2016 ዓ/ም
ዕውቀት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አሥፈፃሚ
ለበለጠ መረጃ